ለመጀመሪያ ጊዜ በህትመት ቴክኖሎጂ የሰለጠኑ ተማሪዎች ተመረቁ

ጥር 21/2014 (ዋልታ) ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በህትመት ቴክኖሎጂ ያሰለጠናቸውን 31 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ ለሶስት ዓመታት በ‘ደረጃ ሶስት’ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታሁን ዋለ ድርጅቱ ለአንድ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያን መደበኛና ሚስጥራዊ ህትመት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በዘርፉ ከሰለጠነ የሰው ኃይል ጋር አጣምሮ በመስራት አገሪቱ ለህትመት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቅረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ በመደበኛነት ከሚያሰለጥናቸው ተማሪዎች በተጨማሪ ከ1 ሺሕ 300 በላይ ለሚሆኑ ሰልጣኞች አጫጭር ኮርሶች መስጠቱንም ተናግረዋል።
መስከረም 14 ቀን 1914 ዓ.ም የተመሰረተው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት 100ኛ ዓመት በዓሉን ለመከላከያ ሰራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግና የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን ማክበሩን የኢዜአ ዘገባ አስታውሷል።