ለመጭው መኸር የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው- የአማራ ግብርና ቢሮ

መጋቢት 01/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ለመጭው የመኸር ወቅት ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ከወዲሁ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የግብርና ግብዓትና የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ተወካይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት ለ2013/14 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 7 ሚሊየን ማዳበሪያ የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው።

ለምርት ወቅቱ ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታሉ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ መግባቱን ተናግረዋል።

ወደ ክልሉ ከገባው ማዳበሪያ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታሉ በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።

ማዳበሪያው የክረምት ወቅቱ ከመግባቱ በፊት የመንገድ አማራጭ በሌለባቸው አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎችና ቀድመው ሰብል በሚያለሙ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል።

ቀሪውን ማዳበሪያ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓም ሙሉ በሙሉ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።