ለምርጫው የሚዘጋጀው የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል መተግበሪያ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል እያበለፀገ ያለውን መተግበሪያ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ አብዮት ለሚታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መተግበሪያው ተሻሽሎ እየበለጸገ ያለው ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ከእጅ ንክኪ ነጻ ለማድረግ ነው።

መተግበሪያውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ ምርጫ ቦርድና ብሮድካስት ባለስልጣን በጋራ እያዘጋጁት መሆኑንም ተናግረዋል።

“የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መገናኛ ብዙሃንና የተመደበውን የአየር ሠዓት ወደ ሲስተሙ በማስገባት መተግበሪያው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ቀመር መሰረት ለእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲና ሚዲያ የተዘጋጀውን ሠዓት ይደለድላል” ብለዋል።

መተግበሪያው የሰው ጉልበት፣ ጊዜና ሀብት በመቆጠብ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችና መገናኛ ብዙሀን በድልድሉ መሰረት መረጃቸውን በፍጥነት እንዲያገኙም ያስችላል።

ቴክኖሎጂው መገናኛ ብዙሃን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ለማንና በየትኛው ሠዓት መስጠት እንዳለባቸው ጊዜ ሳይፈጁ ለማወቅ እንደሚያስችላቸውም ተገልጿል።

መተግበሪያ መተግበሪያው በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ጥቅም የዋለ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ነው አቶ አብዮት የገለጹት።

መተግበሪያው በ2007 ዓ.ም በአጭር ጊዜና በችኮላ በመዘጋጀቱ ያልተካተቱ ክልሎችና ቋንቋዎች እንደነበሩበት አቶ አብዮት አስታውሰዋል።