ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰላም የሀገር መሰረት ነው፤ ይህ ከኢትዮጵያውያን የተደበቀ ሀቅ አይደለም፤ ለሰላም ዋጋ ሲሉ ኢትዮጵያውያን ብዙ መስዋዕነት ከፍለዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ መፅሐፍ ቅዱስ ጥናት የተዘጋጀው መድረክ “ስለ ሀገራችን ሰላም ዕድገትና አንድነት በመተባበር እንስራ” የሚል የሚል የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ሰላምን በሚያውክ እብሪተኛ ስብስብ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟን አጥታለች በማለት ሰላም ተባባሪ ጓደኛ ትፈልጋለች፤ እብሪተኖችንም ትጠላለች ሲሉ ገልፀዋል።
ዘላቂ ሰላምና ፀጥታዋ የተጠበቀ የበለፀገች ሀገርን ለማስቀጠል ሀገር በምትፈልገን አውድ ሁሉ በግምባር ቀደምትነት መሰለፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የመለያየትና የግጭት ሂደቶች ተለውጠው ዘላቂ ሰላም በሀገሪቱ ለማስፈን በሚያስችልበት ሁኔታ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ከ200 በላይ አለም አቀፍ የመፅሐፍ ቅዱስ ማህበራትን አካቶ በያዘው የመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር አባል ሲሆን ላለፉት 97 ዓመታት ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማርና መፅሐፍትን በማሳተም ትውልድን ሲያንፅ የቆየ ማህበር ነው።
በሃኒ አበበ