ለሰሜን ወሎና ዋግ አካባቢ ተፈናቃዮች በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ ድጋፍ ሊሰባሰብ ነው

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) – ለሰሜን ወሎና ዋግ አካባቢ ተፈናቃዮች ቅዳሜ እና እሁድ በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ ድጋፍ ሊሰባሰብ ነው::

በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በደሴ እና በኮምቦልቻ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ ገርጂ ካምፓስ ነገ ቅዳሜ እና ከነገ ወዲያ እሁድ የአይነት ድጋፍ ይሰበሰባል።

የሰሜን ወሎ እና ዋግ አካባቢ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ በአዲስ አበባ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር እያዩ ሉልሰገድ ማንኛውም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ደረቅ ምግብ አልባሳት እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመያዝ በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ ግቢ እንዲገኝ ጥሪ አቅርበዋል።

በነገው እለት ማለትም ከነሃሴ 15- 16/2013 ዓ.ም በሚቆየው የሁለት ቀናት የአይነት ድጋፍ ማሰባሰቢያ ስነስርዓት የሚገኙ ድጋፎችን በመያዝ አዲስ አበባ የተቋቋመው ኮሚቴ በመጭው ሳምንት ተፈናቃዮች ወደ ሚገኙባቸው የደሴና ኮምቦልቻ  ከተሞች እንደሚያመራ ዶ/ር እያዩ ሉልሰገድ ተናግረዋል።