ለሰራዊቱ የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጋሞ ዞን አስተዳደር ገለፀ

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – አሸባው የህወሓት ቡድን ሙሉ ለሙሉ እስኪደመሰስ ለመከላከያ ሰራዊት የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጋሞ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

አሸባሪውን  ቡድን የሚያወግዝና መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ  ሰብስቤ ቡናቤ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመመለስ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን እና የውጭ ሀገራት ተፅእኖን በመቋቋም ሀገራዊ ምርጫ እና ሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት በማጠናቀቋ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

አንድነት እና ህብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር አሸባሪው ቡድን እስኪደመሰስ ድረስ ለመከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳና የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባለብዙ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ከታሪኳ እንደምንረዳው ለማንም ተፅዕኖ የማትንበረከክ እና በህዝቦቿ አንድነት ጠላቶቿን የምታሸንፍ ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ዛሬ ላይ ያለን እኛም የሀገሪቱን ያለፈ ታሪክ ከማውራት ባሻገር ጁንታው ቡድን እስኪደመሰስ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሞራል እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ታሪክ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ለየመከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡

የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ገመዳ ጀግኖች አባቶች የፋሽስት ጣሊያንን ወራሪ ዘር ሐይማኖት ሳይለዩ ድል እንዳደረጉ አስታውሰው  የዛሬ ወጣትም በሀገሪቱ ላይ የተቃጣውን ጦርነት በመቃወም እና በመዝመት ዳር ድንበራችን እንዲያስከብር ጠይቀዋል ።

የህጻናት ፓርላማ ምክትል አፈጉባኤ ህጻን ብሩክታዊት አለማየሁ ህጻናት እህትና ወንድሞቻችን  በመማሪያ ዕድሜያቸው ለጦርነት እየተሳተፉ እየሞቱ ነው ብላለች።

ህጻናት በለጋ እድሜያቸው ተምረው የነገዋን ኢትዮጵያ መረከብ እንጂ የጦር መሣሪያ ተሸክመው ለሞት በመሰለፋቸው ማዘናቸውን በጋሞ ዞን ህጻናት ፓርላማ ስም ሀዘኗን መግለጿን ከዞኑ ኮምዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።