ለሽብር ቡድኑ እያገዙ ትግራይ ክልሌ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ማለት አይቻልም- አቶ ገብረጻዲቅ ገብረመድህን

አቶ ገብረጻዲቅ ገብረመድህን

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – ለሽብር ቡድኑ እያገዙ ትግራይ ክልሌ ነው፤ ኢትዮጵያም ሀገሬ ነች ማለት የሚያዋጣ አይደለም ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ገብረጻዲቅ ገብረመድህን ገለጹ፡፡

አቶ ገብረጻዲቅ ገብረመድህን ዛሬ ሀገር ስትፈልጋቸው ጀርባቸውን ሰጥተው ለሽብር ቡድኑ የሚያግዙ አካላት በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መስዋእትነት አሸባሪው ህወሓት ሲወገድ፤ ትግራይ ክልሌ ነው ኢትዮጵያ ሀገሬ ነው ሊሉ እንደማይችሉና ተጠያቂነት እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡

የጁንታው ኔትወርክ ስላልተበጠሰ በትግራይ የሚገኙ ዜጎች ለመከላከያ ድጋፋቸውንም ሆነ ለጁንታው ተቃውሞአቸውን ቢያሳዩ እርምጃ ስለሚወስድባቸው ሀሳባቸውን መግለጽ እንደ ማይችሉም አቶ ገብረጻዲቅ አስታውቀዋል።

በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር ለወገናቸው መቆማቸውን ከሞራል ድጋፍ ጀምሮ ገንዘብ እና የሚያስፈልጉ ነገሮችን በመሰብሰብ ለሀገር እና ለወገን ሊደርሱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ አሸባሪው ህወሓት በከፋፍለህ ግዛ ሴራ ካልሰራ ማደር አይችልም ያሉት አቶ ገብረጻዲቅ፣ ኢትዮጵያውያን ካልተከፋፈሉ ወደ አንድነት ይመጣሉ፤ አንድ ከሆኑ ደግሞ ስልጣኔን ያሳጡኛል በማለት፤ ኢትዮጵያውያንን መከፋፈል አለብኝ በሚል ሲሰራ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡