ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች በብዛት በመቅረባቸው የበዓል ገበያው እንዲረጋጋ ሆኗል – የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች በብዛት መቅረባቸው የበዓል ገበያው የተረጋጋ እንዲሆን ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ገለፀ።
ከተማ አስተዳደሩ ለበዓል በተለየ መልኩ የገበያ ዋጋ መረጋጋት እንዲችል አስቀድሞ ከአምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር ምርቶች በስፋት እንዲገቡ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።
በዚህም ለዘመን መለወጫ የቁም ከብቶች፣ የእንስሳት ተዋፅኦዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም የተለያዩ የእህል ሰብሎች በሽማች ማኅበራትና በነጋዴዎች በብዛት ማቅረብ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ በዚህ የአዲስ ዓመት በዓል አላግባብ ዋጋ በመጨመር የዋጋ ንረት ለማስከተል የሚሞክሩ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው በርካታ ምርት በማስገባት ገበያው እጥረት እንዳይገጥምና ዋጋውም ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ በሚገኙ የሸማች ኅብረት ስራ ማኅበራት እንዲሁም በየአካባቢው የተቋቋሙ የእሁድ ገበያዎች ሰፊ የገበያ አማራጭ በመሆን የገበያውን ሚዛን መጠበቅ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
አሁንም ኅብረተሰቡ ከእነዚህ አማራጪች በመሸመት ከህገወጥ ነጋዴዎች ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡