ለኅልውና ዘመቻው ከ3.3 ቢሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን የአማራ ክልል ድጋፍ አሰባሳቢ ግብርኃይል አስታወቀ

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) ለኅልውና ዘመቻው ከ3.3 ቢሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን የአማራ ክልል የኅልውና ዘመቻው ድጋፍ አሰባሳቢ ግብርኃይል አስታወቀ፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና የኅልውና ዘመቻው የገንዘብ አሰባሳቢ ግብርኃይል ሰብሳቢ አማረ ሰጤ የኅልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት የሚሠበሰበው ድጋፍ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ሽብርተኛው የሕወሓት ወራሪ ኃይል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ ውድመቶችን አድርሷል፤ ማኅበረሰቡም የኅልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

እስካሁንም ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከከተማ ነዋሪው፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ በክልሉ ካሉ የልማት ድርጅቶች እና ሠራተኞች፣ ከፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልሉ ቢሮዎች እንዲሁም ከዲያስፖራው 3 ቢሊየን 320 ሚሊዮን 55 ሺኅ ብር በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ምክትል አፈ ጉባኤው እና የኅልውና ዘመቻው የገንዘብ አሰባሳቢ ግብርኃይል ሰብሳቢ አማረ የሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ስንቅ ለማቅረብ 67 ሺሕ 52 ኩንታል ስኳርን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች፣

56 ሺሕ 837 ካርቶን ብስኩት፣ ከ10 ሺሕ በላይ ሰንጋዎች፣ በጎችና ፍየሎች፣ 178 ሺሕ 585 ደርዘን ጁስ እና ውኃ ከማኅበረሰቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን የከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ሁሉም ኃላፊነቱን በትጋት መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በገንዘብ እና በዓይነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ 2.1 ሚሊየን ሕዝብ ተፈናቅሎ ይገኛል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ተፈናቃዮችን ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ማኅበረሰቡ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ በባንክ ከተከፈቱ አካውንቶች በተጨማሪ በተከፈተው የቴሌ ኤስ ኤም ኤስ 9595 ገቢ በማድረግ መደገፍ እንደሚቻልም መግለፃቸውን አሚኮ ዘግቧል።