ለአህጉራዊ ሰላም የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተሞክሮ መውሰድ አለባቸው ተባለ

ሰኔ 5/2014 (ዋልታ) ለአህጉራዊ ሰላም ሌሎች የአፍሪካ አገራትም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ተሞክሮ በመውሰድ በጋራ መደራጀትና መሥራት እንዳለባቸው በአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናርዶስ በቀለ ገለፁ።

በአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ዋና ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በተቋሙ የተሠሩ የለውጥ ሥራዎችን በተለይም ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል የሚገለገልባቸው ቴክኖሎጂዎችና ትጥቆች እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ፎረንሲክ ዲፓርትመንት አዳዲስ የቴክኖሎጂ አቅሞችን ተዘዋውረው እንዲመለከቱ አድረገዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናርዶስ በቀለ ለልማት ዋናው መሠረት ሕግ ማስከበር መሆኑንና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተጠቀመበት የሚገኘው ቴክኖሎጂ ሕግን ለማስከበር ጉልህ ሚና አለው ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል፣ ሰላምን ለማስፈንና እድገትን ለማፋጠን በራስ አቅም ሥራዎች መሰራቱ እንዳስደሰታቸው የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ የተመለከቱት ቴክኖሎጂ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡