የካቲት 27/2014 (ዋልታ) በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ለተሾሙ አምባሳደሮች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቋል።
ዛሬ በተካሄደው የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተገኙ ሲሆን አዳዲሶቹ አምባሳደሮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በሚመደቡባቸው አገራት ሁሉ የኢትዮጵያን ትክክለለኛ ገጽታ ለዓለም በማስታዋወቅ ወንድማማችነትን በመፍጠር ዓለም ኢትዮጵያን እንዲረዳ የማድረግ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የዓለምን ነበራዊ ሁኔታ ያገናዘበና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገርን የሚያኮራ ሥራ እንዲያከናውኑም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ሥልጠናውን የተከታተሉ አምባሳደሮች ሥልጠናው የአገሪቷንና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንደተሰጣቸውና በዚህም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በእውቀት ለመፈጸም እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
የአምባሳደርነት ሥራቸውንም በአግባቡ ለመፈጸም ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸውን ኢፕድ አስነብቧል።