ለአሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ ገቦች ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ለአሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ ገቦች ሀሰተኛ ሰነዶችና ማስረጃዎችን ሲያዘጋጁ የነበሩ 13 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ሰባቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የወሳኝ ኩነት ሰራተኞች ሲሆኑ፤ ስድስቱ ደግሞ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ሕገወጥ ማስረጃዎቹን ሲያዘጋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ናቸው ተብሏል።

የጸጥታ አካሉ ባደረገው ፍተሻም 81 የሚደርሱ የመንግስትና የግል ተቋማትን ተመሳስለው የተዘጋጁ ሐሰተኛ ክብና የራስጌ ማሕተሞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ማህተሞቹ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማትን ተመሳስለው የተዘጋጁ መሆኑንም ነው የተገለፀው።

በአዲስ አበባ ፖሊስ የሙስና እና ገቢዎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዳይሬክተር ኮማንደር ደሪቤ ገዳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ግለሰቦቹ ሐሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

በዚህም ፖሊስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊርማና ማህተም ማረጋገጫ፣ ተከፍሏል የሚሉ የአየር መንገድ ክብ ማህተሞች፣ የተማሪዎች የትምህርት ማስረጃ፣ የፓስፖርትና መንጃፍቃድ እና ሌሎችንም ተመሳስለው የተዘጋጁ ማሕተሞችና ማስረጃዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ በአንድ መታወቂያ እስከ 10 ሺህ ብር ሲቀበሉ እንደነበር አመልክተው፤ በወንጀሉ ከተጠረጠሩት ውስጥ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት 262 ሺህ 840 ብር በፍተሻ መያዙን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።