ለአብሮነታችን እና ለፍቅራችን እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

ሚያዝያ 30/2014 (ዋልታ) ለአብሮነታችን እና ለፍቅራችን እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ “የሰላምና የአብሮነት ከተማ” በሚል መሪ ሀሳብ ኅብረተሰብ ዐቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአካል ብቃት እንቅስቃሴው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “አዲስ አበባ የሰላም ፣ የፍቅር ፣ የአብሮነትና የኢትያዊነት መገለጫ ከተማ ናት፡፡ በአብሮነታችንም እናደርጋታለን” ብለዋል።
ሁላችንም በጋራ በያለንበት አካባቢ የኅብረተሰብ ዐቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ልማድ በማድረግ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባልም ብለዋል።
ለአብሮነታችን እና ለፍቅራችን እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ያሉት ከንቲባዋ የግጭት ነጋዴዎች በፍፁም አዲስ አበባ ላይ ሊፈነጩ አይችሉም ብለዋል፡፡
ሕዝቦቿ በፍቅር አብሮነት ያለምንም ልዩነት አብሮ የመኖር ምሳሌ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡