ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ልዩ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላት

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ

ኅዳር 5/2015 (ዋልታ) የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ለኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበርክቶላታል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በተሰማሩበት የሥራ መስክ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 78 የኮሚሽኑ ስፖርት ክለብ አባላት የማዕረግ፣ የገንዘብና የልዩ ኒሻን ሽልማት አበርክቷል፡፡

በሽልማት ፕሮግራሙ ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ልዩ የኒሻን ሽልማት የተበረከተላት ሲሆን አትሌቷ በተሰጣት ሽልማት መደሰቷን ገልጻ በማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ትንሽ ልጅ ሆና በመቀጠር አሁን ለደረሰችበት ደረጃ መብቃቷንም አንስታለች፡፡

ሽልማቱ የማረሚያ ስፖርት ክለብ ወጣት አትሌቶች ጠንክረው እንዲሰሩ፣ እንዲበረታቱና የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ያደርጋል ያለችው አትሌቷ በተለያዩ የውድድር መስኮች የኮሚሽኑ አትሌቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

ኮሚሽኑ ለ34 ስፖርተኞች ከረዳት ሳጅን እስከ ኮማንደር ድረስ የማዕረግ ዕድገት ሲሰጥ ለ19 ስፖርተኞች ደግሞ የገንዘብ እና ለ13 ስፖርተኞች የእርከን ጭማሪና የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል፡፡

ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተበረከተው ልዩ የሜዳሊያ ሽልማት ከረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ቀጥሎ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW