“ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ” ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ በመቀናጀት የሚሠሩት “ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ” ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን “ኢትዮጵያ ታምርት” እና የኤጀንሲውን “አዲስ ለልጆቿ”ን በማቀናጀት ይፋ የሆነው ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ ፕሮጀክት የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ያለመ ነው ተብሏል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ከ25 ከመቶ በላይ ዜጎቿ ትምህርት ቤት የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ከ8 ሺሕ በላይ ጫማዎችን ለተማሪዎች፣ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ጫማ ደግሞ ለፀጥታ ኃይሎች በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው መቅረባቸውን አንስተዋል።

ዘንድሮም የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ ፕሮጀክትን በመጠቀም ለ799 ሺሕ 930 ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ለ30 ሺሕ መምህራን ጋውን፣ ከ350 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ጫማን ለማቅረብ ታቅዷል።

ይህንንም ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባለፈ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ማስፋት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ባለፈ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለማስፋት ይሠራል ብለዋል።

ወላጆች ልጆቻቸው በሀገራቸው ምርት እንዲኮሩ እንዲያስተምሩ፤ አምራቾችም የምርት ጥራታቸውን አሻሽለው እንዲቀርቡ ጥሪ ቀርቧል።

በመርኃ ግብሩ በተለያዩ ሥራዎች ለፕሮጀክቱ እውን መሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በትዕግስት ዘላለም