ለአንድ ወር የሚቆይ መጽሀፍት ማሰባሰብ መርኃግብር ይፋ ሆነ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) “ሚሊየን መፃህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ መፅሀፍት መፅሀፍ ለማሰባሰብ እቅድ መያዙ ተነግሯል።

የመፅሀፍት ማሰባሰብ ሂደቱ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29 የሚቆይ እንደሚሆንም የአዲስአበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) መፅሃፍት የማሰባሰቡ ዋነኛ ዓላማ መፅሃፍትን በዓይነትና በብዛት ማሰባሰብ፣ አንባቢና ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠርና ለሌሌች ክልሎችና ከተሞች የሚሆን መፅሀፍትን ማሰባሰብ ነው።

ይህንን እቅድ ለማሳካትም በጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት፣ የአዲስአበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከአምስት ተቋማት የተውጣጡ ኮሚቴዎች የመሪነት ሚናውን ይጫወታሉ  ተብሏል።

ከነዚህ ተቋማት በተጨማሪ በአንድ ወር በሚኖረው የመፅሀፍት ማሰባሰብ ሂደት የተቋማት፣ የማህበራትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ስያሜ  በመስጠት መፅሀፍት የማሰባሰቡም ስራ ይከናወናል ተብሏል።

ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል መፅሃፍት እንዲለግስና አንባቢ ትውልድን በማነፁ ሂደት የበኩሉን አሻራ እንዲያኖርም ጥሪ ቀርቧል።

በትዕግስት ዘላለም