ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች አዲስ ልዩ ሰሌዳ መውሰድ እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አስታወቀ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች አሁን የለጠፉትን ሰሌዳ በመመለስ አዲስ ልዩ ሰሌዳ መውሰድ እንደሚገባቸው የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አሁን ላይ በተግባር የሚስተዋለው ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች አዲሱን ልዩ ሰሌዳ እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ በዚህ የተነሳ አካል ጉዳተኞች ሊያገኙ የሚገባቸውን አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ብሏል።

በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞች በቀረጥ ነፃ መብት ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው የሚገለገሉባቸውን ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለው ህገወጥ ተግባርና ክፍተት ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።

አንዳንድ የመብቱ ተጠቃሚዎች መብታቸውን ላልተፈቀደለት ህገ ወጥ ተግባር እየተጠቀሙና ተሽከርካሪዎችን ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፍ መንግሥት ተገቢውን ታክስና ቀረጥ እንዳያገኝ መደረጉንም ሚኒስቴሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ይህን ለማስቆምና የመብቱ ተጠቃሚዎች የሚገባቸውን እገዛ እንዲያገኙ ለማድረግ ተሽከርካሪዎቹ ልዩ ሰሌዳ ለጥፈው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ተግባር ለመቅረፍና የቀረጥ ነፃ መብቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ብቻ ለማድረግ የመመሪያውን ድንጋጌ ላይ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል።

መንግሥት የአካል ጉዳተኛ ዜጎች በመንገድ ትራንስፓርት አገልግሎት ላይ የሚደርስባቸውን እንግልት ለመቅረፍ ባመቻቸው እድል የመብቱ ተጠቃሚዎች የቤት ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ አስገብተው ለራሳቸው ብቻ እንዲጠቀሙ መመሪያ ቁጥር 41/2007 በ2007 ዓ.ም ማውጣቱ ይታወሳል።

በሱራፌል መንግስቴ