ለአገር ደህንነት ስጋት በሚሆኑ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የህዝብን ሰላምና ፀጥታ የሚያውኩና ጦርነት በመቀስቀስ ለአገር ደህንነት ስጋት በሚሆኑ አካላት ላይ የጸጥታ ኃይሉ ጥብቅ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ህብረት ሥልጠና ዋና ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንን ገለጹ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅና የምክክር፣ የጥናትና ትብብር ማዕከል በጋራ ያዘጋጁት “የፀጥታ አካላት ለውጥ፣ የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል የተዘጋጀው ፓናል በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንን፤ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ ከፖለቲካዊ አመለካከትና ወገንተኛነት ነጻ የሆነ እንዲሁም የአገርን ጥቅም የሚያስቀድም የፀጥታ ተቋማት ሪፎርም መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱን ወቅታዊ የፀጥታና ደህንነት ስጋቶች ታሳቢ ያደረገ ጥልቅ የለውጥ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ በሥልጠና እና አደረጃጀት የጸጥታ ተቋማት ጠንካራ እንዲሆኑ ተደርጓልም ብለዋል።

የጸጥታ ተቋማቱ በሀገር ላይ የተሞከሩ ውጫዊና ውስጣዊ አፍራሽ ሙከራዎችን በመቀልበስ ያስመዘገቡት አኩሪ ተግባርም የዚሁ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ቡልቲ ታደሰ፤ የፀጥታ ኃይሎችን አደረጃጀትና ቀጣይነት ለመወሰን የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነቱ በመርህ ላይ መመስረቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ሆኖም ወታደራዊ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሲቪል አመራሩና ወታደራዊ አመራሩ ባላቸው የተለያየ እይታ፣ የትኩረት አቅጣጫና የግዳጅ አፈጻጸም አማራጮች ላይ በቀላሉ ለመግባባት ሲቸገሩ ይስተዋላል ብለዋል።

በሲቪልና ወታደራዊ ግንኙነት መርህ ላይ ግልፅ የሆነ መረዳት ባለመኖሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ የአፍሪካ አገራት ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት ሲሉም አስረድተዋል።

በመሆኑም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።

“የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት የአንድ ሀገር መከላከያ ሰራዊት እንደ ተቋም በሥልጣን ላይ ካለው መንግስትና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያለውን የሚያግባባ የትስስር መሰረት የሚያመለክት ነው” ያሉት ደግሞ የምክክር የጥናትና ትብብር ማዕከል የቦርድ አባል አምባሳደር ተቀዳ አለሙ ናቸው።

በኢትዮጵያና በሌሎችም በሰለጠኑት ሀገራት ጭምር በሲቪልና ወታደራዊ ግንኙነት ዙሪያ በሠራዊቱም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ የለም ሲሉ ተናግረዋል።

የሲቪልና ወታደራዊ ግንኙነቱን በየጊዜው ከሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ቴክኖሎጂካዊና ጂኦፖለቲካዊ ለውጦች አንጻር በየወቅቱ በመፈተሽ ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ስኬታማ ተግባር ማከናወኗን የተናገሩት ሌተናል ጄነራል ይመር፤ በሪፎርሙም ይህን ስኬት ይበልጥ ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

የፀጥታ ተቋማት ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

የብሔር ጥላቻን በማራገብ የሕዝብ ሰላምና ፀጥታ የሚያናጉ፣ ጦርነትን የሚቀሰቅሱ፣ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚሰሩ አካላትን በሕግ መቆጣጠርና ስርዓት ማስያዝ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለሌሎች አገራት ሰላም የምትሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፀጥታ ኃይሉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን ማጠናከር ይጠበቅበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውይይት መድረኩ የፀጥታ አካላት ለውጥና የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት፣ የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ ወቅታዊ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን የሚዳስሱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ጄነራል መኮንኖች፣ የክልልና የፌደራል የፀጥታ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቀድሞ ጦር ሠራዊት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡