የካቲት 7/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በቂ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።
በዚህም በቂ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ የ60 ቀናት ዕቅድ በማውጣት ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡
የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ለህብረቱ ጉባኤ የአጀብ እና የጸጥታ ስራዎች ወታደራዊ የተግባር ላይ ልምምድ በስኬት ማከናወኑንም አስታውሰዋል፡፡
36ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ “የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከጉባዔው ቀደም ብሎ የካቲት 8 እና 9 የውጭ ጉዳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚያደርጉ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም ለህብረቱ ስብሰባ የሚመጡ እንግዶች በአጀብም ሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ህብረተሰቡ የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ተብሏል፡፡
ህብረተሰቡ በማንኛውም ወቅት ከፀጥታ ስራ ጋር ተያያዥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት እና ማንኛውንም የፖሊስ አገልግሎቶችን ለማግኘት በስልክ ቁጥር 01-11-11-01-11 አልያም በ991 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በሰለሞን በየነ