ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት መከበር የአፋር ክልል ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የካቲት 02/2014 (ዋልታ) የአፋር ክልል ሕዝብ ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው አስቸጋሪ አገራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት መከበር ፈተናዎችን በመጋፈጥ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቷ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በሰመራ ከተማ ተወያይተዋል።

በዚህም ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው አስቸጋሪ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ የአፋር ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት መከበር ፈተናዎችን በመጋፈጥ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል ብለዋል።

በዚህ ሂደት ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ዜጎች ህይወት ጠፍቷል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው በአገሪቱ የተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ሰብኣዊ ጉዳት ማስከተሉንና በተለይም ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም አቅመ ደካሞችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩ በውይይትና በመግባባት እንዲፈታ ድርጅታቸው የድርሻውን ይወጣል ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በተጨማሪም መንግሥታቱ አፋርን ጨምሮ በአገሪቱ በጦርነቱና ተያያዥ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን ሰብኣዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተባበሩት መንግሥታት የልማት አጋር በመሆን በክልሉ ለተገኙ እድገትና ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች መስፋፋት የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።