ግንቦት 04/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገው የ1442ኛው የኢድ-አልፈጥር በዓል የኢድ ሶላት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ለጊዜው ለተሽከርካሪ ዝግ የሆኑ መንገዶችን ይፋ አደረገ፡፡
በዚህም ከ22 ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከወሎ ሰፈር ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከመስቀል ፍላወር አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከኮካ ኮላ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከበርበሬ በረንዳ በቀድሞው 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ መስቀል አደባባይ፤ ከቀድሞው ፈረሰኛ ፖሊስ በጌጃ ሰፈር ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ ከተክለኃይማኖት በጥቁር አንበሳ ወደ ጎማ ቁጠባ፣ ከአትላስ ወደ ኡራኤል ቤተክርስቲያን የሚወስዱ መንገዶች ከማለዳው 11፡30 ሰዓት ጀምሮ ለትራፊክ ዝግ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
አሽከርካሪዎችም ይህን አውቀው አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ተባባሪ እንዲሆኑና በተገለፁት መንገዶች ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በዓሉ ካለአንዳች የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞቱን በመግለጽ፣ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙና ለማንኛውም ፖሊሳዊ አገልግሎት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ስልክ ቁጥሮች 011-1-11-01-11 እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር መጠቀም እንደሚቻል አሳስቧል፡፡