መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር በሺህ የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገባው መሆኑን እና በተቀናጀ መንገድ ጫናውን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡
የዋጋ ግሽበቱ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ሲሆን፣ ይህም ስግብግብ ነጋዴዎች እያደረጉት ባለው የዋጋ ጭማሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዜጎች ከገቢያቸው ለምግብ ነክ ወጪ 60 በመቶ፣ ለመኖሪያ ቤት ከ16 እስከ 20 በመቶ፣ እንዲሁም ለአልባሳት ከ3 እስከ 5 በመቶ ወጪ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡
ይህንን በተለይ ከምግብ ነክ ሸቀጦች ጋር ተያይዞ ያሉ ወጪዎችን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ስራ መጀመርን አንስተው፣ አርሶ አደሩ የበጋ ስንዴን በመስኖ የማልማት ዘዴን በመጠቀም ለዋጋ ንረቱ መቀነስ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
ከኩታ ገጠም እርሻ በተጨማሪ የበጋ መስኖ እርሻን ማስፋፋት ከቻልን በግርናው ዘርፍ ከፍተኛ እድገትን በማስመዝገብ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ በቢሊየን የሚቆጠር ብር ወጪ በማድረግ የተጀመሩ ከ200 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቁም አስረድተዋል፡፡