ለዓመታት ሽብርተኛውን የሸኔ ታጣቂ ኃይል ሲያገለግል እና ሲመራ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) ለዓመታት ሽብርተኛውን የሸኔ ታጣቂ ኃይል ሲያገለግል እና ሲመራ የነበረ እያሱ ዓለሙ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

ግለሰቡ በታጣቂ ኃይሉ ውስጥ አባል ሆኖ በቆየባቸው ዓመታት በውጪ ሀገራት ጭምር የተለያዩ ሥልጠናዎች መውሰዱን እና ለጥፋት ተልዕኮ ተሰማርቶ መቆየቱን ተናግሯል።

በ2007 ዓ.ም ታጣቂ ቡድኑን እንደተቀላቀለ እና በቆየባቸው የጥፋት ዓመታት ከተራ ተዋጊ እስከ ሎጀስቲክስ ኃላፊነት እንደሠራ የገለጸው ወጣት እያሱ የጥፋት ቡድኑ በእንግሊዝ ሀገር የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት እንዲከታተል እና ተመልሶ የሽብርተኛውን አባላት እንዲያሰለጥን እንዳደረገው ገልጿል።

ወጣት እያሱ በሽብርተኛው ሸኔ የጥፋት ተልዕኮ በቆየባቸው ዓመታትም የጥፋት ቡድኑን ከሚደግፉ አካላት ከ15 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር ድረስ ተቀብሎ ለታጣቂ ኃይሉ አመራሮች የማድረስ ተግባር እንደፈፀመ ተናግሯል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር በሽብር ሥራዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበረው ወጣት እያሱ መንግሥት ለታጣቂ ኃይሉ ይቅርታ ባደረገበት ወቅት የዕድሉ ተጠቃሚ ሆኖ በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሃድሶ ሥልጠና እንደወሰደ እና ሥልጠናውን እጠናቆ እንደወጣም በታጣቂ ኃይሎች አስገዳጅነት እንደገና የሽብርተኛው አባል እንደሆነ አስረድቷል።

ግልሰቡ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት በኅብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉ ነው የተገለጸው።

በሽብርተኛው ቡድን የሚነገርው የሐሰት ውዥንብር እና መሬት ላይ ያለው እውነት እንደማይገናኝ ወጣት እያሱ መናገሩን በመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ገልጿል።

የደቡብ ዕዝ በቀጣናው በሚያከናውናቸው የሰላም ጥበቃ ሥራዎች ወጣት እያሱን ጨምሮ 4 የሸኔ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።