ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ከ500 ሚሊየን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ500 ሚሊየን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጭነት “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት 3 ዓመታት ተካሂዷል።

በየዓመቱ 92 ሺሕ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺሕ ሄክታር ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል ተብሏል።

የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንደገለጹት መርኃ ግብሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ያስችላል።

ይህም ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ጠቅሰው ላለፉት ሦስት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ተመናምኖ የነበረው የተፈጥሮ ኃብት እንዲያገግም መደረጉን ገልጸዋል።

መርኃ ግብሩ የተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ እንደ አንድ አጀንዳ ሆኖ በሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቁመዋል።

አሁን በመላው ሀገሪቱ ያሉት የችግኝ ጣቢያዎችም 120 ሺሕ መድረሳቸውን ገልጸው ይህም በሥራ ፈጠራ ረገድ በርካታ የሥራ እድልን መፍጠር የቻለ መሆኑን አመላክተዋል።

አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና አፕል በዋናነት ለምግብነት ከሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በዘንድሮው የችግኝ ተከላ የሚተከሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ችግኞች በቀጣዮቹ ዓመታት ራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድጉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅቱ ለችግኝ ተከላ ምቹ እንደሆነና ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ያሳየውን መነቃቃት እንዲደግመውም ጠይቀዋል።