ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ

 

ሚያዝያ 17/2015 (ዋልታ) በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

በየዓመቱ የበጀት የጊዜ ዑደቱን ጠብቆ የሚደረገው የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ሰሚ የተጀመረ ሲሆን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱን የ2016 በጀት በመስማት መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡

ፕሮግራሙን በሚኒስቴሩ ያስጀመሩት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመደበኛና የካፒታል በጀታቸውን በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት ማቅረብ አንዳለባቸው አመልክተው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸውን በጀት በአግባቡና በቁጠባ የመጠቀም ኃላፊነት አንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ጥረቱን የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበለጠ ውጤት የሚያስመዘግቡበትን ስልት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ተቋማቱ በሂደት ላይ ያሉ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም ማሳሰባቸውን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል::