ለደቡብ ዕዝ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ማልበስ መርሃግብር እየተካሄደ ነው

የካቲት 6/2014 (ዋልታ) በመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እና የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ የሠራዊት አባላት የሜዳሊያ ሽልማትና የማዕረግ ማልበስ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

የማዕረግ ዕድገቱ የባለ ሌላ ማዕረግ መስመራዊ መኮንን እና ከፍተኛ መኮንን እንደሚያካትት ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።

የማዕረግ አሰጣጥ ሥነስርዓቱ ለ33 የዕዙ አባላት ከምክትል አስር አለቃ እስከ ሙሉ ኮሎኔል ማዕረግ የማልበስ ሥነስርዓት እየተካሄደ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

መርሃግብሩ በመከላከያ ሠራዊት የብሄራዊ ተጠባባቂ ኃይል ማደራጃና ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ኢተፋ ራጋን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በተገኙበት እየተከናወነ ነው።