ለገላን ቱሉ ጉራቻ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ የሚሆን ድጋፍ ተደረገ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ለገላን ቱሉ ጉራቻ 1ኛ ደረጃ ትምህርት  ቤት 300 ሺሕ ብር የሚገመት የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ቢሮው ለተማሪዎች ምገባ አገልግሎት የሚውሉ ግብአቶችን ያበረከተ ሲሆን፤ የምግብ ዘይት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ፣ ዱቄት በተጨማሪ የደብተር፣ ስክሪፕቶ እና ቦርሳ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሰርካአለም ሳኩሜ እንደተናገሩት በዛሬው እለት የተደረገው የትምህርት እና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ከ300 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ነው።

ቢሮው በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ላይ የሚሰራ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ኃላፊዋ፤ የክልሉ መንግስት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመገብ እቅድ ማውጣቱን ተከትሎ ለአንድ ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተናግረዋል።

የቱሉ ጉራቻ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት አዛለች ወንድሙ በበኩላቸው፤ ለተማሪዎች ምገባ የሚደረገው ድጋፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ የሚያስችል በመሆኑ የተማሪዎችን ብክነት ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በገላን ከተማ 10 ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን አምስቱ የተማሪ ምገባ ፕሮግራም መጀመራቸውን የከተማው ከንቲባ ወይንሸት ግዛው ተናግረዋል።

በአስቴር ጌታሁን