ለገና ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

ታኅሣሥ 18/2014 (ዋልታ) ለገና ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ዓብይ ኮሚቴ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከታኅሣሥ 20 ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጿል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በያለበት ሁሉ የኢትዮጵያን እውነታ ለማሳወቅ ያደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው አሁንም ለሀገራቸው ያላቸውን አለኝታነት ለማረጋገጥ ወደ ሀገራቸው ለመግባት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንግዶች በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች በሚኖራቸው ቆይታ በጦርነቱ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከመጎብኝት አንስቶ ባዛሮች፣ ፌስቲቫሎችና ሌሎችም ኹነቶች መዘጋጀታቸውንም ኮሚቴው አስታውቋል።
በመስከረም ቸርነት