ለግሸን ደብረከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል ቅድመ ዝግጅት

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) የግሸን ደብረከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ለማክበር አስተማማኝ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ እንደገለጹት፤ ለግሸን ደብረከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል ኢትዮጵያዊያን ከአራቱም ማዕዘናት መጥተው የሚያከብሩት ነው።

የንግስ በዓሉን በአስተማማኝ መንገድ እንዲከበር ከደብሩ አስተዳዳሪዎች፣ ከዞኑ አመራሮች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ጸረ-ህዝብና ጸረ-ቅርስ የሆነውን አሸባሪው ህወሃት በቅርሶችና በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጽመው ድርጊት አስነዋሪና የሚወገዝ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ በግሸን ደብር ከርቤ በዓሉን ለማክበር አስተማማኝ የጸጥታና ሌሎች ዝግጅቶች መደረጋቸውን አመላክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ያለምንም ስጋት ለሚናፈሰው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሳይሸበር ወደ ግሸን መጥተው በደማቅ ሁኔታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዞኑ ነዋሪ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በዓሉን ለማጠልሸት የሚመጣ ጸጉረ ልውጥ ሲያጋጥም ለጸጥታ ኃይሉ ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሳራ ስዩም