ለ1 ሺሕ 100 አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርኃግብር ተካሄደ


ሚያዝያ 4/2014 (ዋልታ) በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የዐቢይና የረመዳን የፆም ወቅትን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺሕ 100 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ እና አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርኃግብር ተካሄደ።

‹‹በጎነት ለዘላቂ ወንድማማችነት›› በሚል መሪ ሀሳብ ነው ከሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ እና በኑሯቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ አቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎች ማዕድ ያጋራው።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ድርጅት ዘርፍ ኃላፊ ተተካ በቀለ በማዕድ ማጋራቱ መርኃግብር ላይ እንደተናገሩት በከተማዋ ያለውን የሕይወት ጉስቁልና እና ችግር ለመዋጋት አስተዳደሩ ውጤታማ የሚሆን የከተማ ግብርና ሥራን እንዲሁም ህገ-ወጥነትን የመከላከል ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ ነው።

የማዕድ ማጋራት ወርቃማ ባሕል አቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመርዳት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበው ለዐቢይ እና የረመዳን የፆም ወራት መዳረሻ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል ረዲ በበኩላቸው በጎነትን ለማሳየት ሀብት የማይጠይቅ በመሆኑ ካለን ላይ በማካፈል ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች ክፍለ ከተማ አስተዳደሩ እና በጎ ፍቃደኞች በዚህ የፆም ወቅት ስላሰቡን እና ድጋፍ ስላደረጉልን እናመሠግናለን ማለታቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW