ለ10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮች የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ 10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮች ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ።

የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ተፈራርመዋል።

በድጋፍ ስምምነቱ መሠረትም የጃፓን መንግስት 185 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮችን እንደሚያበረክት ተገልጿል።

ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮቹ ሙሉ የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችን የሚያሟሉ መሆናቸው ተመላክቷል።

ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮቹ በጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮች እና በተለያዩ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በድጋፍ ስምምነቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተገኝተዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW