ለ12ኛ ክፍል ፈተና የሚውሉ 450 ሺህ ታብሌቶች እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ከውጭ እንደሚገቡ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
በኦንላይን የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና እስከ ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ለመስጠት ዕቅድ መያዙን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ዝግጅት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) በትምህርት ቤቶች ላይ ተተክለው ከሚኒስቴሩና የፈተናዎች ኤጀንሲ ሰርቨሮች ጋር የሚገናኙ 1 ሺህ 500 ቪሳት ቴክኖሎጂ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መሳሪያዎቹን የሚተክሉ 250 ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
12 ሺህ ላፕቶፖች ደግሞ ለፈታኞች ለማከፋፈል ዝግጁ እንደሆኑ ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ 450 ሺህ ታብሌቶች ደግሞ እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ከውጭ እንደሚገቡ መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።