ለ49 ሺሕ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ሊሰጣቸው መሆኑ ተገለጸ

ጃንጥራር አባይ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ለ49 ሺሕ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ሊሰጣቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በከተማዋ ለሚገኙ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል አጠናቀው ሥራ ለሚፈልጉ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እንደሚሰጥ የገለጸው ቢሮው ስልጠና ከሚሰጣቸው መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም አመላክቷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመት የሚቆይ እንደሆነ ገልጸው በፕሮጀክቱ ከ49 ሺሕ በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚካሄድ የገለጹት ኃላፊው እስካሁን ከ27 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ተመልምለው መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

እየተጠናቀቀ ባለው የመጀመሪያ ዙር በጀት ዓመት ከ10 ሺሕ 500 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደና ሁለተኛው ዙር በሚቀጥለው 2015 ዓ.ም የሚቀጥል እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህም እድል ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች በሚፈልጉት ቀላል ሙያ በመሰልጠን በቀላሉ የኪስ ገንዘብ እያገኙ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያገኙ በማድረግ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥርላቸው ሲሆን ከዚህም ውጭ በራሳቸው የሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እውቀት የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል።

በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክቱ በ11 ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን አዲስ አበባ ትልቁን ድርሻ ትይዛለችም ነው የተባለው።

በሚልኪያስ አዱኛ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW