ለ7ኛ ጊዜ የአዲስ አበባ ጤና ባለሙያዎች ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገላቸው

ጥቅምት 03/2013 (ዋልታ) ለ7ኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሆስፒታሎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በህልውና ዘመቻ ላይ ለሚገኙት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ልዩ ኃይል ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ሽኝት ተደረገ።

የጤና ባለሙያዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እና በቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ እንዲሁም የቢሮው ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

የጤና ባለሙያዎች በህልውና ዘመቻው ላይ ሙያዊ አገልግሎት በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑም ተገልጿል።

የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በሽኝቱ ወቅት በሀገራችን የተቃጣውን የህልውና ዘመቻ ለመመከት ለተሰማራው የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ኃይል የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ በምንም ሊተካ እንደማይችል ገልጸዋል።

ኃላፊው የጤና ባለሙያዎች ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት በመወሰን ለሚያደርጉት አገልግሎት አመስግነዋል።

አክለውም ቢሮውም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ሁሌም ይኮራባችኃል ከጎናችሁ በመሆንም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደረጋል ማለታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡