ልማት ባንክ ለኢንተርፕራይዞች ስልጠና መስጠት ጀመረ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሦስተኛው ዙር የቀጠለ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና መስጠት ጀመረ።

“በእውቀት የተደገፈ ተወዳዳሪ እና ሥራ ፈጣሪ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ለሀገር እድገት መሰረት ነው” በሚል መሪ ሃሳብ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ኢንተርፕራይዞችን በእውቀት እና ክህሎት በማገዝ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ያስችላል ተብላል።

አምራች የሰው ኃይልን በመጠቀም የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት እውቀትን መሰረት ያደረገ ሥራ መከወን እንደሚገባም ተጠቅሷል።

ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ ጨርሰው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተደራጅተው ወደ ልማት እንደሚገቡም ይጠበቃል።

ስልጠናው በወላይታ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳር እየተሰጠ ይገኛልም ነው የተባለው።

በባሕር ዳር ከተማ በሦስት የስልጠና ማዕከላት 4 ሺሕ 189 ሰልጣኖች ስልጠናውን እስከ ግንቦት 12 እንደሚወስዱም ተጠቅሷል።

በሀኒ አበበ