ልማት ባንክ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በወረኢሉ ወረዳ በጦርነቱ ለተጎዱ በሦስት ቀበሌዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች 100 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 10 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች እና 4 መለስተኛ ዘመናዊ ትራክተሮችን ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ወረኢሉ በአገሩ ክብር የማይደራደር ጀግና ሕዝብ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ በተደረገው የኅልውና ጦርነት ተጋድሎ በማድረግ መዋጋቱን እና ጀብድም መፈፀሙን ተናግረዋል።

በወረዳው የደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት የከፋ ቢሆንም ማኅበረሰቡ ለሥራ ካለው ጥንካሬ እና የአካባቢው ሰብል አምራችነትን ታሳቢ በማድረግ ባንኩ ተገቢውን የግብዓት እና ቴክኖሎጅ ድጋፍ እያደረገ ወረኢሉን ሞዴል አድርጎ ለማስቀጠል እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የወረኢሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሰለሞን አይቸው፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላደረገው ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

ለመስኖም ሆነ ለመኸር እርሻ ምቹ መሬት እና ውኃ ባለው ወረኢሉ ግብርናውን ለማዘመን ልማት ባንክ በጀመረው ሁኔታ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተው እንደሚሰሩ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።