ልዩነቶችን በይደር መፍታት የስልጡን ፖለቲካ አካሄድ ነው- አቶ ቀጀላ መርዳሳ

አቶ ቀጀላ መርዳሳ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ ልዩነቶችን በሂደት ለማጥበብ ያደረጉት እንቅስቃሴ የስልጡን ፖለቲካ አካሄድ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ አስታወቁ፡፡

አቶ ቀጀላ እንደገለጹት በፓርቲዎቹ መካከል የተለያዩ የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩም ልዩነቶቻቸውን በይደር ለመፍታት ወስነው በጋራ ጉዳይ ላይ ለመስራት መስማማታቸው በአገሪቱ ታሪካዊ ከመሆኑም በላይ የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡

ፓርቲያቸው እንደማንኛውም ፓርቲ ጥያቄ ቢኖረውም ጥያቄዎቹ በሂደት እንደሚፈቱ በማመን መንግሥት በጋራ ለመስራት ያቀረበላቸውን ጥያቄ በአዎንታ እንደተቀበሉት ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል መንግሥት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሀገር ጉዳይ ላይ እንደሚያሳትፍ ሲገልጽ ፓርቲያቸው ሂደቱን እንደ አበረታች ጅምር በደስታ ማየቱን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል፡፡

መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ጠላት ከመተያየት ውጭ አብረው መስራት የማይታሰብ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአዲስ መልክ የተመሰረተው መንግሥት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት መሞከሩ የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡