ልዩ የስነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት ማዕከል በጅማ ዞን ማረሚያ ቤቶች ተከፈተ

መስከረም 27/2014 (ዋልታ) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከልና የጅማ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በመተባበር ልዩ የስነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት የህክምና ማዕከል በጅማ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ግቢ ዉስጥ ተከፈተ፡፡

በማዕከሉ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ ዓሊ የስነ-አዕምሮ ጤና አገልግሎት አሰጣጡን በማሳደግና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የምርመራ ማዕከሉ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሚሰጠው አገልግሎት የተሟላ እና ቀጣይነት ያለዉ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና ግብዓቶችን ድጋፍ በማድረግ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በጅማ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የማረምና የማነጽ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ሳጂን አብዱራዛቅ ያሲን በበኩላቸዉ ከዚህን በፊት ታራሚዎችን ለስነ-አዕምሮ ጤና ምርመራ ምልልስ በሚደረግበት ጊዜ ተጠርጣሪዎች ከህግ ጥላ ስር የማምለጥ፤ተጨማሪ ወንጀል የመስራት ሙከራ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ማእከሉ በጊቢ ዉስጥ መከፈቱ ችግሩን መፍታት ማስቻሉንና አላስፈላጊ የሆኑ የወጪ፤የጊዜ እና የጉልበት ብክነትን ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጅማ ጤና ኢንስቲትዩት የክሊኒካል ቺፍ ዳይሬክተር ዶ/ር ፈቲያ አወል የተጀመረዉን ሥራ ለማጠናከር ያለንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅመን ለዉጤታማነቱ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በተለይ በዘርፉ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን በአግባቡ በመጠቀም አገልግሎቱን በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነን ማለታቸውን ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ህክማና ማዕከል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።