ልደተ ክርስቶስ በድምቀት የሚከበርባት ላሊበላ ዝግጅቷን አጠናቃለች

ታኅሣሥ 28/2014 (ዋልታ) ልደተ ክርስቶስ በድምቀት የሚከበርባት ላሊበላ ከሰዓታት በኋላ ለሚጀመረው የዋዜማ አከባበር ዝግጁ መሆኗ ተገለፀ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በድምቀት የሚከበርበት የሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ቤዛ ኩሉ ዓለም የሚባል ወረብና ዝማሬም በልዩ የሚቀርብበት ነው፡፡

ይሀም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ እረኞች እና መላዕክት ያመሰገኑትን ምሳሌ በማድረግ እንደሆነ የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ፡፡

በላሊበላ የሚከበረው ገና በአከባበሩም ሆነ በዝማሬው በሌሎች አካባቢዎች ከሚከወኑ ሽብሸባዎች ለየት የሚል፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተጨማሪ የቅዱስ ላሊበላ ልደትም የሚከበርበት ቀን ነው፡፡

የሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ መምህር ይደርሳል መልሴ ሕዝቡ ከአሸባሪው የትሕነግ ወራራ ኃይል ተላቆ በዓሉን ለማክበር በመዘጋጀቱ ደስተኛ መሆኑን ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

ምንይሉ ደስይበለው (ከላሊበላ)