ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የአል-ሸባብ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር- ሸኔ ታጣቂዎችን ከቀጠናው ቢያስወግዱ የሁለቱ አገራት ሕብረት እንደሚጠናከር ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት በሞያሌ የተገነባውን የድንበር መተላለፊያ ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በመሆን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።
“አል-ሸባብ እና ኦነግን ከቀጠናው ብናስወግድ ሕብረታችን ይጠነክራል” ብለው ተናገሩ ሲሆን ኦነግ ሲሉ ኦነግ-ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ቡድንን እንደሆነ የጠቅላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ገልጸዋል።
ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከኦነግ ተገንጥሎ በመውጣት በምዕራብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በምትዋሰንበት ደቡባዊ ክፍል የትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ይነገራል።
ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በቀጠናው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የአካባቢው ደህንነት ማረጋገጥ ግድ መሆኑን ተናግረዋል።
“የደኅንነት ችግር እያለብን ኢኮኖሚያዊ ድል ማስመዝገብ አይቻለንም” ያሉት ፕሬዝደንት ኡሁሩ፤ “እንደ ሁለት ጎረቤት አገራት በውስጣችን እየኖሩ የኢትዮጵያንም የኬንያንም ሰላም የሚያውኩት ላይ መስራት ይኖርብናል” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንሰትሩ “መሰረተ ልማቶች ላይ በጋራ እንደምንሰራው ሁሉ የአከባቢውን ደህንነት ለማረጋገጥ እንድንሰራ” ለፕሬዝደንት ኡሁሩ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል።
(ምንጭ፡-ቢቢሲ)