ሕወሓት በአገር ኅልውና ላይ የደቀነውን አደጋ በተባበረ ክንድ መቀልበስ አለብን – የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

ናትናኤል ፈለቀ

ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በአገር ኅልውና ላይ የደቀነውን አደጋ ሁሉም ወገን በተባበረ ክንድ መቀልበስ እንደሚኖርበት የኢዜማ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ አመለከቱ፡፡

ፓርቲው አባላቶቹና ደጋፊዎቹ ወደ ግንባር እንዲዘምቱና ለትግሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም የበኩሉን እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለኢፕድ እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ አሸባሪው ሕወሓት በአገር ኅልውና ላይ ፈርጀ ብዙ አደጋዎችን ደቅኗል፡፡

ቡድኑ የኢትዮጵያን ህዝብ የመኖር ዋስትና እየተፈታተነ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር ዋስትናውንና የሀገሩን ህልውና ለማረጋገጥ ሁሉም ወገን በተባበረ ክንድ አሸባሪውን ሕወሓት ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም ለጊዜው ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አመላክተው የፖለቲካ አመለካከትን በነጻነት ማራመድ የሚቻለው አገር ስትኖርና ሰላም ሲሰፍን መሆኑን ገልጸዋል፡፡