ሕወሓት ጦርነቱን እንደጀመረ ያረጋገጠ ዓለም ዐቀፍ ሪፖርት ይፋ ሆነ

 ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ሌሊት በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመክፈት ዛሬ አንድ ዓመት የሞላውን የኢትዮጵያ ጦርነት እንደጀመረ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የጥምር ምርመራ ሪፖርት አስታወቀ፡፡
ሁለቱ ተቋማት ምርመራ ያደረጉት ከጥቅምት 24/2013 እስከ ሰኔ 21 ድረስ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ላይ ሲሆን ዋና ትኩረቱን ትግራይ ክልል ውስጥ ያደረገ ነው፡፡
ምርመራው አስፈላጊ ናቸው በተባሉና የሽብር ቡድኑ ጥቃት የሰነዘረባቸውን የጎንደርና ባሕር ዳር አየር ማረፊያዎች ማካተቱ የተገለፀ ሲሆን በአጠቃለይ ሪፖርቱ 269 የጥቃት ሰለባዎች፣ የአይን እማኞችና ሌሎች ምንጮችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡
የጦርነቱ ጀማሪ ሕወሓት መሆኑን ያሳወቀው የጋራ ምርመራ ሪፖርቱ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም እንደጀመረው ነው ማረጋገጫን የሰጠው፡፡
በዚህም የፌደራሉ መንግሥት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉኣላዊነትን ለማስከበርና ከጥቃት ራሱን ለመከላከል ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን አመልክቷል፡፡
ከመንግሥት የሰላም ጥሪ በተጨማሪ በአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሰላም ፈላጊ እናቶች ተደጋጋሚ ልዩነትን በሰላምና ውይይት የመፍታት አዋጭ መፍትሔን እንዲከተል በልመናም ጭምር ሲጠየቅ የነበረው የሽር ቡድን አሻፈረኝ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
ይልቁንም ሰላምና እርቅ ፍለጋ የሄዱ እናቶችን፣ የሃይማኖት መሪዎችንና የአገር ሽማግሌዎችን በትዕቢት ተወጥረውሲያመናጭቁም ጭምር የነበሩት የሽብር ቡድኑ መሪዎች የጦርነት ነጋሪትን ሲደልቁ፤ ወታደራዊ ትርኢት ማሳየትን ሰርካዊ ተግባራቸው አድርገውት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ጦርነቱን በይፋ ከጀመሩት በኋላም የቡድኑ አፈ ቀላጤዎች ስለጦርነቱ ጀማሪና ያደረሱትን ጥቃት በተመለከተ ዕርስ በዕርስ የሚጋጭ መረጃን ሲሰጡ ነበር፡፡ በቅርቡም የአሸባሪው መሪ ደብረፂዮን ጦርነቱን ተገደን ጀመርን ሲል ሌላው አጋሩ ፃድቃን ገብረትንሳኤ ጦርነቱን አስበውበትና መርጠውት እንደጀመሩት ተናግሯል፡፡