ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አደሀ በዓልን አቅመ ደካሞችን በመርዳት እንዲያሳልፍ የእስልምና ሀይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

ሐምሌ 1/2014 (ዋልታ) ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አደሀ /አረፋ/ በዓልን አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመጠየቅ እንዲያሳልፍ የእስልምና ሀይማኖት አባቶች ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ እና ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ጥሪ አቀረቡ

ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ እና ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ 1 ሺሕ 443ኛውን የኢድ አል አደሀ/አረፋ በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ነገ በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን ታላቁን የኢድ አል አደሀ /የአረፋ በዓል በሰላም ወጥቶ አክብሮ በሰላም እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡

ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ እና ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኢዜአ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ሰላም የሁሉም መሰረት በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ታላቁ የኢድ አል አደሀ /አረፋ በዓል በፍቅር፣በአንድነትና በወንድማማችነት እንዲከበር ሕዝበ ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

አገር፣ ቤተሰብ፣ልማትና እድገት የሚኖረው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለሰላም ከፍ ያለ ዋጋ በመስጠት በሰዎች መካከል የትብብርና ወንድማማችነት መንፈስ ማስፈን ይገባል ብለዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የአረፋ በዓል ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣የተራቡትን በማብላት፣የታረዙትን በማልበስ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

ሀይማኖት የሚኖረው ሀገር ሲኖር መሆኑን በመረዳት በዓሉን ስናከብር በመተዛዘን፣በመረዳዳትና አንድነትን በማጠናከር መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶቹ 1 ሺሕ 443ኛው የኢድ አል አደሀ/አረፋ በዓል የሰላም የደስታ የብልጽግናና የመከባበር ይሆን ዘንድ የትብብር መንፈስ መጎልበት አለበት ብለዋል፡፡