ሕዝቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ እየሆነው ነው ተባለ

ደጀን ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበር

ነሀሴ 22/2013 (ዋልታ) – ደጀን የሆነው ሕዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ ላይ ለሚገኘው ሠራዊት የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የብርጌድ መሪዎች ገለፁ።

በጎንደር ከተማ የሚገኘው “ደጀን ለኢትዮጵያ” የበጎ አድራጎት ማኅበር በግንባር በመገኘት ለሠራዊቱ የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ማኅበሩ በተገኘበት ግንባር ሠራዊቱ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን የመደምሰስ ግዳጁን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የብርጌድ መሪዎቹ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍም አሸባሪውን ቡድን እየደመሰሰ ላለው ሠራዊት የሞራል ስንቅ ሆኗል ብለዋል።

“ደጀን ለኢትዮጵያ” ማኅበር ይህንን በመረዳት ግንባር ድረስ በመገኘት ለሠራዊቱ ላደረገው ድጋፍና ላሳየው ደጀንነት የብርጌድ መሪዎቹ አመስግነዋል።

የአገር ሕልውና ማስከበር ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

ሠራዊቱ ሕዝብ የሚገድለውን፣ የሚዘርፈውንና የሚወረውን አሸባሪ ቡድን እየደመሰሰ መሆኑንም የብርጌድ መሪዎቹ ተናግረዋል።

ሠራዊቱ የሕልውና ዘመቻውን በድል እንዲያጠናቅቅ የሕዝቡ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የ”ደጀን ለኢትዮጵያ” አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ አያሌው ማኅበሩ አሸባሪው ህወሓት አገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት ለመመከት እየተጉ ያሉትን የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና የፀጥታ አካላትን ለመደገፍ መቋቋሙን ነው የገለጹት።

ግንባር ድረስ በመሄድ “ድጋፍ ያደረግነው ሠራዊቱ እየከፈለ ያለውን ዋጋ በመገንዘብ ያለንን ክብር ለመግለፅ ነው” ብለዋል።

በቀጣይም በሌሎች ግንባሮች ለሚገኙ የሠራዊት አባላት ደጀንነታቸውን ለማሳየት ድጋፍ እንደሚያደርጉም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።