ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚፈጠሩ ዕድሎችን ወደ ጥቅም ለመለወጥ በቱሪዝም መዳረሻ ኢንቨስትመንት ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን ዳያስፖራዎች ተናገሩ።
ከዓመታት በፊት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተከትሎ የመዝናኛ ከተሞች እንደሚመሰረቱ መንግስት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከሰሞኑ በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድጋፍ የሕዳሴ ግድቡን የጎበኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ልዑክ በግድቡ ዙሪያ በጉባ ሰማይ ስር ስላሉ የነገዎቹን የቱሪስት መዳረሻ ዕድሎችን ቃኝቷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የልዑኩ አባላት እስካሁን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብም ሆነ በሌሎች ተሳትፎዎች ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአሜሪካ ቴክሳስ ነዋሪው የቀድሞ ፖሊስ ሠራዊት አባል መቶ አለቃ ንጉሴ ሲገኝ ከኢትዮጵያ ከተሰደዱ 41 ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ አባይ ለአገር ብልጽግና ሊውል መቃረቡን ተመልክቻለሁ ይላሉ።
የግብጽና ሱዳን የስልጣኔ መነሻ በሆነው አባይ ወንዝ ለዘመናት በብቸኝነት ሲጠቀሙ መኖራቸውን አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ከአባይ ውሃ ለመጠቀም ወደሚጨበጥ ተስፋ ተሸጋግራች ነው ያሉት።
ለግድቡ ስኬት ከሶስት ዓመታት በፊት በተጀመረው በቀን አንድ ዶላር ገቢ በሚደረግበት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ መቶ አለቃ ንጉሴ በዓመት አንድ ጊዜ 365 ዶላር በመዋጣት አሻራቸውን ያሳርፋሉ።
በአገር ውስጥ ከመቀነታቸው እየፈቱ የሚከፍሉ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ሁሉ ዳያስፖራው ደግሞ አነስተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ ቢለግስ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የለንደን ነዋሪው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ ዳያስፖራው በየሙያው ኢትዮጵያን ማገዝ ስላለበት በተለይ የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች የሚፈጥሩትን ውዥንብር በማጥራት በሚዲያ መስክ ሲሰራ መቆየቱን ይገልጻል።
ግድቡን በአካል ከተመለከተ በኋላ በአባይ ጉዳይ በሙያው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጠው።
የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላቱ ግድቡ ለፍጻሜ እስኪበቃ ከሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ባሻገር ግንባታው ሲጠናቀቅ በሚፈጠሩ የቱሪዝም መዳረሻ ኢንቨስትመንቶች አሻራቸውን እንደሚያሳርፉም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባልና የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪው አቶ አለማየሁ ስለሺ ግድቡ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር በቱሪዝም መዳረሻነት ሌሎች ጸጋዎቸን ይዞ ይመጣል ይላሉ።
ሰው ሰራሽ ሐይቁ የሚፈጥራቸውን የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች ማልማትና ለአካባቢው ነዋሪ የስራ ዕድል መፍጠር በተለይም ብዙ ልምድና ሐብት ካካበተው ዳያስፖራው ትልቅ ሃላፊነት ይጠበቃል ብለዋል።
ከ21 ዓመታት በኋላ ከካሊፎሪኒያ ወደ እናት አገራቸው የተመለሱት አቶ ሙሉጌታ ምህረትም ግድቡ ሲጠናቀቅ ለስፖርት መዝናኛነትና ለቱሪስት መዳረሻነት ፋይዳው ጉልህ በመሆኑ አሁንም ቀጣይንት ያለው ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከሜሪላንድ የመጡት ሲስተር ማርታ ገብረስላሴ የኢትዮጵያዊያን የነገ ተስፋ ከግድቡ ጀርባ መሆኑን ገልጸው፤ ግድቡን በአካል በማየታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚመጡ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድሎች በሌሎች አገራት እንደሚታዩት ትልቅ አቅም እንዳላቸውና በዚህ ረገድ የግድቡን መልከ ብዙ ፋይዳ ተረድቶ ዳያስፖራው በሁሉም መስክ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል።