ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመሰረቱ ለማስቀረት በዚህ ዓመት የማኅበረሰብ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በድንበሮች አካባቢ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የነበረው ቁጥጥር በመላላቱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መጨመሩ ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰብሳቢነት የሚመሩት ብሔራዊ የሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሕገወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ብሔራዊ ምክር ቤት የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ ስብሰባውን አካሂዷል።
በውይይቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በድንበሮች አካካቢ የነበረው ቁጥጥር የሰዎችን ፍልሰት ቀንሶት እንደነበር ተነስቷል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድንበሮች አካባቢ ቁጥጥር መቀነሱ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት እየሆነ ነው ተብሏል።
በወረርሽኙ ሳቢያ በርካታ አገራት ድንበራቸውን መዝጋታቸውና የውጭ አገር የስራ ስምሪትም መቋረጡ ለሕገወጥ ስደት መጨመር ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
አብዛኞቹ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደሆኑም ተመልክቷል።
በሕጋዊ ፈቃድ ሽፋን በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር የተሰማሩ አካላት መኖራቸውም በውይይቱ ተነስቷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ወንጀል ከምንጩ ለማድረቅ የማኅበረሰብ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የማኅበረሰብ ንቅናቄ በኤች.አይ.ቪ እና በኮቪድ ወቅት ያመጣውን ለውጥ ለአብነት በማንሳት ማኅበረሰቡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እንዲጠየፍና እንዲያወግዝ ንቅናቄ መካሄድ አለበት ብለዋል።
ለንቅናቄው የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እድሮችና ሌሎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን አካላት መጠቀም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በአገሪቷ የሚገኙ ቀበሌዎችን ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነጻ ማውጣት የንቅናቄ ዘመቻው አካል መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ንቅናቄው ውጤት ተኮር፣ የታቀደና የሚሰሩ ስራዎችም በተጨባጭ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ክልሎች በቅንጅት እንዲሰሩ ያስገነዘቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃላፊነቱን የማይወጣ ተጠያቂ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ብሔራዊ የሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሕገወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር ብሔራዊ ምክር ቤት በ2007 ዓ.ም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል የተቋቋመ መሆኑን አስታውሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡