መሀል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መሥጠት ጀመረ

ጥር 23/2014 (ዋልታ) በአሸባሪውና ዘራፊው የሕወሓት ቡድን ጉዳት ደርሶበት የሕክምና አገልግሎት ያቋረጠው የመሀል ሜዳ ሆስፒታል በተደረገለት ድጋፍ አገልግሎት መሥጠት ጀመረ፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሉ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በአካባቢው ማኅበረሰብ በተደረገለት ድጋፍ የሕክምና አገልግሎት መሥጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ወርቅነህ ዘዉዴ ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ሆስፒታሉ በተደረገለት የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት ድጋፍ የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎት፣ የድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን አገልግሎት እንዲሁም የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎቶችን መሥጠት ጀምሯል፡፡
በየዕለቱ በአማካይ ከ150 እስከ 200 ታካሚዎች አገልግሎት እያገኙ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡
ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በመሀል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሠሩ የህክምና ባለሙያዎች የአምቡላንስ አገልግሎት በመስተጓጎሉ በእናቶችና በድንገተኛ ጤና አገልግሎት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያኘነው መረጃ ያመለክታል::