መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የቀድሞ ሰራዊት አባላትና ምልምል ሰልጣኞች ገለጹ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) አገሪቱን ከአሸባሪው ለመታደግ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ በብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚያሰለጥኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት እና የ35ኛ ዙር ምልምል ሰልጣኞች ገለጹ፡፡

ሻምበል ፈለቀ ደበሌ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት 102ኛ ክፍለ ጦር አየር ወለድ አባል ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት የመንግስትን ጥሪ በመቀበል በብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሻምበል አዛዥ በመሆን ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

“በደል ደርሶብን ከሰራዊቱ ብንገለልም በአገር ድርድር ስለሌለ ዛሬም አገሪቱን ከባንዳዎች ለማዳን  ወራሪውን ኃይል ለመፋለም ዝግጁ ነኝ” ብለዋል፡፡

ምክትል መቶ አለቃ ቀለምወርቅ ድረስ በበኩላቸው ሳይወዱ በግድ ከሚወዱት የውትድርና ሙያ መሰናበታቸውን አውስተው የእናት አገር ጥሪ ተቀብለው ወደ ሙያቸው በመመለሳቸው መደሰታቸውንና አገሪቷ ወደነበረችበት ሰላም ለመመለስ ማንኛውንም መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ምልምል ሰልጣኞቹ የሚሰጣቸውን ስልጠና በላቀ ውጤት በማጠናቀቅ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በጀግንነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡