“መንግሥት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታውን ለመወጣት ህግን አክብሮ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ይሠራል” – የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) “መንግሥት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታውን ለመወጣት ህግን አክብሮ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ይሠራል” ሲል የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተደቀነብንን ህልውናችንን እና ሉዓላዊነታችንን የማጣት አደጋ ለመቀልበስ ስንል ሙሉ ትኩረታችንንና ሁለንተናዊ አቅማችንን ተገደን በገባንበት ጦርነት ላይ አውለናል።
ስለ ህልውናችን እና ሉዓላዊነታችን መከበር ሲባል የከፈልነው መስዋእትነት በአይነቱም ሆነ በመጠኑ ያለው ዋጋ ከሀገር አንድነት፣ ክብር እና ቀጣይነት አንጻር ሲታይ ተገቢም አንገብጋቢም ነበር።
በመሆኑም መደበኛ የሆነውን መንግሥታዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት መደበኛ ያልሆኑ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ጭምር በዘመቻ ለሕልውና ሂደት ውስጥ መጠቀም አስፈላጊና የተሻለው አማራጭ በመሆኑ በጦርነቱ ሂደት ውስጥ ተተግብሯል።
በውጤቱም በአሸባሪና ወራሪው የሕ.ወ.ሃ.ት ቡድን አማካይነት እንደ አማራ ሕዝብ የተደቀነብንን ሕልውና እና እንደ ሀገር ሉዓላዊነታችንን የማጣት አደጋ ለመቀልበስ አስችሎናል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ሁነት ውስጥ ስለሕዝባቸው ደህንነትና ስለ ሀገር ሉዓላዊነት ሲሉ መሰዋእትነትን የከፈሉ ሁሉ ሰማእት የሆኑለት ሕዝብ እና ሀገራቸው ዘንድ በዘላለማዊ ክብር ሲታወሱ ይኖራሉ።
በአንጻሩ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ከህወሃት በኩል የተሰነዘረበትን ቀጥተኛ ጥቃት ለመቀልበስ በጦርነት ሂደት ውስጥ የነበረበትን ወቅት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከአማራ ሕዝብ ሕልውና ቀጣይነት እና ከሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ማስቀደም መርጠዋል።
በምርጫቸውም መሰረት ለውጫዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ በመሆን በሰርጎገብነት፣ በህገ ወጥ ድርጊትና የአፈና፣ የዝርፊያ፣ የኮንትሮ ባንድ ንግድ፣ የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ የግድያ ወንጀሎችን አንሰራፍተዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ ሁከት፣ ብጥብጥ እና ስርዓት አልበኝነትን በማስፈን ሕዝብ እንዳይረጋጋ እርስ በርሱ እንዲጋጭና አንድነቱን እንዲያጣ የሚያደርጉ ተግባራትን በመፈጸም ራሳቸውን በአማራ ሕዝብ ጉያ ውስጥ የወሸቁ ውሥጣዊ ጠላቶች ሆነው ተገኝተዋል።
የአማራ ሕዝብ በውጭ ጠላቶቹ እንዳይገረሰስ የተዋደቀለትንና እንደ ሕዝብ ያለውን ሕልውና ለማሳጣት ሕገ ወጥነትንና ሥርዓት አልበኝንት በክልሉ ውስጥ እንዲንሰራፋ የማድረግን አፍራሽ ዘዴ እንደ ትግል ስልት ሲጠቀሙበት ተስተውለዋል።
በእነዚሁ አካላት አማካይነት በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች የተፈጸሙት የሕገወጥ እና ሥርዓት አልበኛ ድርጊቶች መበራከት የተንገሸገሸው መላው የክልላችን ሕዝብ መንግሥት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ አቅርቧል።
ለዚህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በተጠና ሁኔታ ተገቢውን ምርመራና በቂ ዝግጅት በማድረግ በክልሉ ውስጥ ሕግና ሥርዓትን ለማንበር ሕጋዊ የእርምት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስፈን እያከናወነ የሚገኘው ተግባር በትእግስት፣ በስክነት እና በህጋዊነት ላይ የተመሰረተ እና ማስተማርን ያስቀደመ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል።
በዚህም ሂደት በርካታዎቹ መንግሥትን አዳምጠውና ክልላዊ ሁኔታችንን ተረድተው ከድርጊታቸው ተቆጥበዋል።
ከጥፋት ድርጊቶች ከመቆጠብም ባሻገርም ከመንግሥት እና ሕዝብ ጎን በመቆም ለገጠሙን ችግሮች ሁሉ የመፍትሔ አካል ሆነው እየሠሩ ይገኛል።
በተቃራኒው አንዳንዶቹ ደግሞ በሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጭምር ለማስመከር የተደረገውን ጥረት እንደ ደካማነት በመቁጠር ከተሰማሩበት የህገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት እንቅስቃሴዎች ለመታረም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው መንግሥት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታውን ለመወጣት ህጋዊ አሠራሩን ተከትሎ የህግ የበላይነትን ለማንበር በትኩረት እንዲሠራ አድርጎታል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የሕግና ሥርዓትን የበላይነት ለማረጋገጥ ካልተቻለው ታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን እየደገሱልን ያለውን የጥፋትና የጦርነት ድግስ በአንድነት ቆመን ለመቀልበስም ሆነ የሕዝባችንን ዘላቂ የልማትና የሰላም ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚቻልበትን እድል ከማምከኑ ባሻገር በሁለንተናዊ መስዋእትነት የተጠበቀውን እና እንደ ሕዝብ ያለንን ሕልውና ሊያሳጣን ይችላል።
በመሆኑም እየተከናወነ የሚገኘው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ መንግሥታዊ ተግባር በዓላማው፣ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ የሕዝብ እና የሀገር ደህንነትን ለማረጋገጥ የታለመ መሆኑን በመገንዘብ መላው የአማራ ሕዝብ ሕግ እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት ሙሉ ውግንናውን በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል።