መንግሥት ለ11ኛው ክልል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መመስረት ለኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት መጠናከር የተሰጠውን ቁርጠኝነትን እንደሚያረጋግጥ መንግሥት ገለፀ፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችየሆኑት የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ፣ የሸካ ሕዝቦችና የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ሕጋዊ ሂደቱን ጠብቀው በሕገ መንግሥቱ የተጎናጸፉትን መብት በመጠቀም 11ኛው የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ሆነዋል ብሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ለበርካታ ዓመታት የክልልነት ጥያቄን ሲያነሱ ቆይተዋል ያለው የመንግሥት መግለጫ የለውጡ አመራር ወደ ሥልጣን እንደመጣ ሲያነሱ የነበረው ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን በማመን ሕጋዊ አካሄድን ተከትሎ እንዲመለስ ጥሯል ብሏል፡፡
ለሕገ መንግሥቱም ሆነ ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንዳች ቦታ ያልነበረውና የዜጎችንም ጥያቄ በማፈን የኖረው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ተግባር ለመቀልበስ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግሥት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡